በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የሚባሉ ቅራኔዎች
‹ወደ ፍርድም አስቀድሞ የገባ ፃድቅ ይመስላል፣ ባላጋራው መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ› ምሳሌ 18.17

የቅራኔዎች መኖር ውንጀላ
በ Jay Smith, Alex Chowdhry, Toby Jepson, James Schaeffer

ክፍል አንድ [ክፍል ሁለት] [ክፍል ሦስት]  [ክፍል አራት]
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ስለሚሏቸው ብዙ ቅራኔዎቸ  ብዙውን ጊዜ ሲያወሩ ይሰማሉ፡፡ እነርሱንም ክርስትንናንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል እንደ ዋነኛ መሳሪያ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ የቅራኔዎቹም ቁጥር የሚለያዩት የምትነጋገሩት ከማን ጋር በመሆኑ ላይ ነው፡፡ ኬራንቪ ኢዛር-ኡል ሃክ የተባለው ሰው 119 ቁጥር ያላቸውን ቅራኔዎች ቆጥሯል ሌሎች ደግሞ እንደ ሻቢር አላይ ያሉት 101 ቅራኔዎችን መዝግበዋል፡፡ እነሱም የሚያነሱት እና በግምት የሚናገሩት ነገር ማንኛውም የሃይማኖት መጽሐፍ እንደሆነ የሚቆጠር ሁሉ በተለይም ከእግዚአብሔር የመጣ የተባለ ምንም ቅራኔ ሊኖረው አይገባም የሚል ነው ምክንያቱም ከመለኮት የመጣ የተባለ መጽሐፍ በራሱ ምንም ተቃርኖ ሊኖረው አይገባምና ነው፡፡

ይህንንም ለማስረዳት ሙስሊሞች ከቁርዓን 4.82 ላይ የሚከተለውን ጥቅስ ይጠቅሳሉ ‹ቁርዓንን አያስተነትኑትምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ዘንድ ብዙን መለያየትን ባገኙ ነበር፡፡›

የእግዚአብሔር መገለጥ ትርጉም:

እንደዚህ ዓይነቱን ተቃውሞ ለመመለስ በቅድሚያ መነሳት ያለብን ከበስተጀርባው ከተነሳበት የመነሻ ሐሳብ ነው፡፡ ምንም ቅራኔ ሊኖር አይገባም የሚለው የአስተሳሰብ መርሆ መሰረት ወደ ፍፁም የሆነ መስፈርት ከፍ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ይህም የእግዚብሔር ቃል በሰዎች ልጆች እንዲፈረድበት በሚያስችል መልኩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ክርስትያኖች የሚስማሙበት ግምትና መነሻ ሐሳብ ሊሆን አይችልም፡፡ ክርስትያን በደስታ የሚስማማው ሀ. ቅዱስ መጽሐፍ በስተፍፃሜው ሁሉ እራሱን የቻለ ለ. ፍፁምና ሐ. ምንም ስህተት የሌለበትና መ. እርስ በእርሱም በምንም ሁኔታ እንደማይቃረን ነው፡፡ በመሆኑም የክርስትያን መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ስህተት የሌለበት ማለትም ህፀፅ አልባ ነው፡፡ “ምንም ተቃርኖ የሌለው” የሚለውን ሐሳብ በተመለከተ ክርስትያኖች የማይስማማመበት ተጨማሪው ሌላው ነገር፣ ይህንን ሐሳብ ይዘው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲፈርዱበት ማድረግንም ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መገለጥ በተመለከተ (በተለይም መጽሐፍ ቅዱስን) ሙስሊሞች በጽሑፎቻቸው ላይ ሊያሰፍሩ ወይንም በውይይት ሊያቀርቡ የሚፈልጉት ነገር ቢኖር ይህንን ነው፡፡

ብዙዎቻችንም የምንወድቅበት ስህተት ይህ ነው፣ ማለትም ለእኛ ትክክል እና ቀጥተኛ የሆነውን ነገር ትክክልና ቀጥተኛ ባልሆነ ነገር ለመለካት መነሳታችን ማለት ነው፡፡ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ቁርአናዊ በሆነ መመዘኛ ለመመዘን መነሳት ማለት ነው፡፡ ወይንም ከቁርአን በተበደርነው መመዘኛ ለመመዘን መነሳታችን ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች እንደሚሉት የእነሱ መጽሐፍ ከሰማይ የተላከ በሰው እጅ ያልተጻፈ ነው፡፡ ይህንን የእነሱን የቅዱስ መጽሐፍ ሐሳብ ማለትም ‹ከላይ የተላከ› የሚለውን ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉት፡፡ ነገር ግን ይህ ለቁርአን የተሰጠው ዓይነት መመሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስም መመዘኛ ተደርጎ መጠቀም አለብን የሚለው የእነሱ ሐሳብ ትክክል አይደለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ሙስሊሞች ለቁርአናቸው እንደሚሉት በአንድ ሰው የተቀናበረ አንድ መጽሐፍ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የ66 መጽሐፍት ቅንብር እና ከአርባ በሚበልጡ ሰዎች በ1500 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህም እውነታ የተነሳ ክርስትያኖች ሁልጊዜ የሚያምኑትና የሚያውቁት አጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው እጅ ጽሑፍ ማህተም ያለበት መሆኑን ነው፡፡ የዚህም ማስረጃ ደግሞ በተለያየ የሰው ቋንቋዎች ጥቅም ላይ መዋልም (መኖርም)፤ የተለያዩ የአጻጻፍ ስነ ዘዴዎች፣ የጸሐፊዎቹ እውቀትና ስሜት ልዩነት፣ እንዲሁም በጸሐፊው ዘመን የነበሩትን ሳይንሳዊና ማህበራዊ ገፅታዎች (ፅንሰ ሐሳቦች) ተፅዕኖ የሚመስሉ ነገሮች መኖራቸውንም ነው፡፡ ያለእነዚህም እውነቶች መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን በተደራሲዎቹ ዘንድ ምንም መረዳት አይኖረውም ነበርና፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለው መጽሐፍ አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ሊያመጣን አይችልም ምክንያቱም ጸሐፊዎቹ እያንዳንዳቸው ከጌታ በቀጥታ የመጣውን የቃልን መገለጥ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ወይንም መሪነት ተቀብለው ነበርና፡፡

የእግዚብሔር እስትንፋስ ትርጉም:

በ2ኛ ጢሞቲዎስ 3.16 ላይ የተነገረን ነገር የእግዚብሔር ቃል በእግዚአብሔር መንፈስ እንደተጻፈ ነው፡፡ (ቃል በቃል ሲተረጎም የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት እንደሆነ ነው)፡፡ ከእግዚብሔር መንፈስ የወጣ የሚለው ቃል ቲዎኑስቶስ የሚል የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‹የእግዚአብሔር እስትንፋስ› ማለት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ቃሉ የመነጨው ከራሱ ከእግዚአብሔር መሆኑን ነው፡፡ በ2ጴጥሮስ 1.21 ላይ ደግሞ የምናነበው ጸሐፊዎቹ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሪት እየተነዱ እንደጻፉት ነው፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱን ጸሐፊ እግዚአብሔር በቀጥታ ተጠቅሞበታል፡፡ ይህንን ታላቅ መለኮታዊ ነገር ለማከናወን፤ እግዚአብሔራዊ ሥልጣን ያለውን መጽሐፍ ለማዘጋጀትና ለመጻፍ እንዲችሉ የተመረጡትን ሰዎች እግዚአብሔር በፀጋው ያስቻላቸው የነበረ ሲሆን፤ በእነሱም ውስጥ በምንም ሁኔታ ሁሉን የሚችለው እግዚአብሔር ስህተትን እንዳላስቀመጠ ግልፅ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ ከመለኮት የመነጨ መሆኑን ብዙ ጊዜ ይናገራል፡ ሉቃስ 24.27፣44 ዮሐንስ 5.39 እና ዕብራውያን 10.7፡፡ ጌታ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ስለእርሱ የተነገረው ነገር እንደሚፈፀም ነው፡፡ ሮሜ 3.2 እና ዕብራውያን 5.12 የሚያሳዩት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ ነው፡፡ በ1ቆሮንቶስ 2.13 ላይ ደግሞ የምናነበው ‹መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊ ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃላ አይደለም› ይህም ደግሞ የሚያጠቃልለው በ2ጢሞቲዎስ 3.16 ላይ ያለውንም ቃል ጭምር ነው፡፡ በ1ተሰሎንቄ 2.13 ላይ ጳውሎስ አስቀድሞ የጻፈውን በመጥቀስ የሚከተለውን ተናግሯል "ስለዚህም የመልክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ ..." በማለት ሲሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ የሐዋርያው ጳውሎስን ጽሑፍ በመንፈስ ቅዱስ መመራት እንደነበረ ሲገልጥ በ2 ጴጥሮስ 3.15-16 ላይ እንደሚከተለው አስቀምጦታል “እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።” ጴጥሮስ ቀደም ብሎም በ2 ጴጥሮስ 1.21 ላይ የጻፈው ‹ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ እንዳልመጣ ነው› ከዚያም በስተመጨረሻ በራዕይ መጽሐፍ ላይ የምናየው ነገር ራዕይ 22.18፣19 ጸሐፊው ዮሐንስ የገለጠው ‹ማንም በዚህ ቃል ላይ ቢጨምርና ቢቀንስ ... › በማለት ነው፡፡

ይህ ነው እንግዲህ በክርስትያኖች ዘንድ ያለው የቅዱስ መጽሐፍት አመለካከት የእግዚአብሔር ቃል የሰው የፈጠራ ውጤት ሳይሆን የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

እግዚአብሔር እንዴት ነበር ጸሐፊዎቹን መገለጥን የሰጣቸው? ጸሐፊዎቹን ወደ አዲስ ከፍታ ላይ እንዲደርሱ ልባቸውን የሚያደፋፍርን ነገር በመስጠት ነበርን? ወይንስ በእነሸክስፒር ሰራዎች ውስጥ እንደምናገኘው በተመሳሳይ መንገድ ነበርን ያደርግ የነበረው?  ሌሎችንም ፀሐፊዎች የነበሩትን ሁሉ መጥቀስ ይቻላል፣ በእርግጥ እንደ እነሱ ነበርን ያደርግ የነበረው? ወይንስ ደግሞ እሱ በመንፈሱ የሰጣቸው ቃል ከተረት ተረት ጋር የተደባለቀ ነበርን? እንዲሁም ደግሞ ስህተቶችና አርበኝነት የሞላባቸው የሰው ጠፊ ቃላት ነበሩ ማለት ነውን? ወይንስ ቅዱስ መጽሐፍት ሙሉ በሙሉ ስህተት የሌለባቸው ዘላለማዊ የሆኑ የቅዱሱ እግዚአብሔር ቃላት ነበሩን? በሌላ አነጋገር ሙስሊሞች እንዴት ነው እነዚህ መገለጦች ተግባራዊ ሆነው ነበር ብለው የሚጠይቁት? እግዚአብሔር መካኒካል የሆነ ዲክቴሽን ‹የቃል ንባብን በማድረግ ነበርን የሰጣቸው ማለትም በቁርአን ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተገለጠው ዓይነት ወይንስ የጸሐፊዎቹን አዕምሮና ልምምድ እንዲሁም ሐሳብ ነበርን የተጠቀመው?

ቀላሉ መልስ የሆነው ነገር በጽሐፉፎቻቸው ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር የበላይ መለኮታዊ ቁጥጥር የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቃል ውስጥ (ወይንም በሰዎች ቃል በኩል) የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነበር ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔር ባህልንና የጸሐፊዎቹን አጠቃላይ ማህበራዊ ሕይወት ተጠቅሞ ነበር እንዲሁም በሉዓላዊ ኃይሉ ነገሮችን ሁሉ ይቆጣጠር ነበርና፡፡ ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት መጽሐፍት መካከል ታሪክ መታየት ያለበት እንደታሪክ፤ ግጥም እንደ ግጥም፤ ምሳሌያዊ አነጋገር እንደምሳሌያዊ አነጋገር፤ ማጠቃለያዎች እንደ ማጠቃለያዎች፤ ግምቶች እንደ ግምቶች ወ.ዘ.ተ ተደርገው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ የነበሩት የሥነ ጽሑፍ ማህበራዊና ባህላዊ አቀራረቦች አሁን በኛ ጊዜ እንዳለው ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ለምሳሌም ያህል ታሪካዊ ቅደም ተከተልን ያልጠበቁ አጻጻፎች፤ በዚያን ጊዜ ተቀባይነት የነበራቸውና ምንም ዓይነት ፍፁም አቀራረብን የማይጠብቁ የነበሩ ከሆነ መወሰድ ያለባቸው ልክ እንደተቀመጠው ተደርጎ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም እነዚህን አቀማመጦች አሁን በምናየው እይታ እንደ ስህተት ልንቆጥራቸው የማይገባን መሆኑን ልናስብበት እና ልንጠነቀቅበት ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የአንድ መልክት ፍፁም የሆነ ዘገባ በማይጠበቅበት እና ባልታቀደበት ጊዜ ያለውን ስህተት የመሰለ ነገር እንደ ስህተት መቀበል እና አድርጎም መቁጠር ትክክል ያልሆነ ነገር ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ምንም ስህተት የለበትም ይህም በዘመናዊ መስፈርት መሠረት እንደሚታየው ሳይሆን የሚለውን ነገር ትክክልነት በማስተላለፍና ጸሐፊዎቹ ባለሙት እና ባቀዱት ባነጣጠሩት እውነት መስፈሪያ መሠረት ጭምር ነው፡፡

የቅዱስ መጽሐፍ እውነተኛነት በውስጡ ባሉት የሰዋስዋዊ ወይንም የቃላት አቀማመጥ መዛባት፤ ወይንም የተፈጥሮ ሁኔታ መግለጫዎች የተምታቱ መምሰል፤ ወይንም የስህተት ሪፖርቶች መኖር (ለምሳሌም የሰይጣን ውሸት ቃሎች ተመዝግቦ መገኘት)፤ ወይንም በአንድ አንቀፅና በሌላው መካከል ባለው የተለያየ ሐሳብን የሚመስል አቀራረብ ላይ ሊወሰን አይችልም፡፡ የሚቃረኑ የሚመስሉ ነገሮች ሊዘነጉ ወይንም ሊዘጉ አይገባቸውም፡፡ ለእነሱም የሚሆን መፍትሄ የመኖሩ ነገር፤ ችግሮቹ ሊደረስባቸው የሚቻል መሆኑንም ማወቅ ለእምነታችን እጅግ ታላቅ የሆነ መበረታቻን የሚሰጠን ነገር ነው፡፡ እንዲሁም እጅግ በጣም መልካም ነው ይህም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በሚገባ ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም መፍትሄ ወይንም የሚያሳምን ማስረጃ ላጣንለት ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን እንደሚገባ እናመሰግነዋለን ምክንያቱም የእሱ ቃል ምንጊዜም እውነት ነውና ይህም ከእነዚህ የተለያዩ ነገሮች የተምታቱ ከሚመስሉ ነገሮች መኖር ባሻገር ነው፤ እናም እኛ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚኖረንን መተማመን ልናጣ አይገባንም ማለት ነው፡፡ ይህም አንድ ቀን እነሱ የተምታቱብን ሆነው ነው የምናገኛቸው ማለትም የእኛ መረዳት ያን ጊዜም እንኳን ቢሆን ትክክል ያልነበረ መሆኑን እናስተውላለን፡፡

ይህ ደግሞ ዝም ብሎ ጭፍን የሆነ ተስፋ ማድረግ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ከመቶ ዓመታት በፊት ስራዎቻቸው ለዶክተሮች ምስጢር የሆኑ 100 የሚሆኑ የሰውነት ክፍሎች ጉዳይ ነበረ፡፡ ስለእነርሱም ያንጊዜ ሰዎች ይሉ የነበረው ‹ይህ የኢቮሉሽን መኖር ማረጋገጫ ነው ምክንያቱም እነዚህ ቅሬተ አካላትና ለምንም የማንፈልጋቸው ናቸውና› በማለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትጋትና ቀጣይነት ባለው ጥናትና ምርምር አሁን ምንም ስራ እንደሌለው በመቆጠር የቀረው አንድ ብቻ የሰውነት አካል ክፍል ነው፡፡  ወደ ፊትም በጊዜውም የዚህ የአካል ክፍል ስራ ምን እንደሆነ እንደሚገኝ እናምናለን፡፡ የዚህ ዓይነት መርሆ ወይንም አካሄድ ነው በመጽሐፍ ቅዱስም በኩል መወሰድ ያለበት፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ቅራኔዎች የመሰሉ ነገሮች ትጋት ባለው ጥናትና ምርምር እንዲሁም መረዳት አማካኝነት አሁን ምንም ቅራኔ እንዳልሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንደ ሻቢር ዓይነት የሙስሊም ተከራካዎች ከ25 ዓመታት በፊት ቢኖሩ ኖሮ ወደ 1001 የሚያህሉ ቅራኔዎች ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች ይዘረዝሩልን ነበር ማለት ነው፡፡ አዲስ ማስረጃዎች እየተገኙ በሄዱ ቁጥር ለብዙ ታሪካዊ ምስጢሮች ያለማቋረጥ መልስ የሚሆንን ነገር እያገኘን ነው፡፡ ስለዚህም ያንን አካሄድ ለማመን የሚያስችሉንን ማንኛውም ዓይነት ምክንያቶች አሉን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ባዘጋጀውም ጊዜ ሌሎቹ የቀሩትም ደግሞ በትክክል መልስን ያገኛሉ፡፡

ክርስትያኖች ስለ መገለጥ ያላቸው የእምነት መስፈርት በሙስሊሞች ተቀባይነት እንደሌለው በትክክል እናውቃለን ምክንያቱም ከእነሱ ጋር የሚቃረን ነው ብለው ስለሚቆጥሩት ወይንም ስለሚመስላቸው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ከናዚል ወይንም ከታንዚል ጋር (ከላይ የተላከ) የሚልና ለቁርአን በሰጡት ፅንሰ ሐሳብ ብቻ፣ ሙስሊሞች እራሳቸውን በድግግሞሽ ይኮንናሉ፣ ይህም አዲስ ኪዳንን የጥንት መገለጥ አይደለም ብለው ሲናገሩ ለቶራህና ለዛቡር ደግሞ በሁሉም ሙስሊሞች በኩል እንደ መገለጥ በመቆጠር ክብር ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሙስሊሞች የሚያምኑት ቶራህን ሙሴ እንደጻፈና ዛቡርን ደግሞ ዳዊት እንደጻፋቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም (ሙሴም ሆነ ዳዊት) የመጣላቸውን መገለጥ በናዚል ወይንም (ከላይ በተላከ) መንገድ እንደመጣላቸው አልተናገሩም፡፡  ስለዚህ በተለይም እራሱ ሰነዱ ምንም እንዲህ ዓይነትን ነገር ሳያሳይ በአዲስ ኪዳን ላይ ለምን እንዲህ አተኮሩ?

መሠረታዊው ምክንያት ያለው በሙስሊሞች እምነት ላይ ነው ያም ቁርአን በሰዎች ጣልቃ ገብነት ያልተፈጠረ ብቸኛ የመለኮት መገለጥ ነው የሚል ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በእነርሱ አባባል ወይንም አመለካከት እውነተኛውና ግልጥ የሆነው የአላህ ቃል ነው ምክንያቱም ከእሱ በፊት የነበሩትን መገለጦችን በሙሉ ይበልጣል እንዲያውም እነዚያን መገለጦችን ሁሉ ይሽራል፡፡ ምክንያቱም በእነርሱ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላቶች እራሳቸው በሰዋዊ ጸሐፊዎቻቸው አማካኝነት በውሱንነት ተበክለዋልና፡፡

ያልተባለው ሌላውና እጅግ በጣም ቁልጭ ያለው አስገራሚ አባባል የቁርዓን “ናዚልነት” የመጣው ከአንድ ምንጭ ብቻ መሆኑ ነው፣ ያም ተገለጠልኝ ብሎ ከተናገረው ሰው ከመሐመድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የመሐመድን አባባል እውነት የሚያደርጉ ሌላ የውጭ ምስክርነቶች ወይንም ምንጮች የሉም፤ ይህም ከመሐመድም ጊዜ በፊት በመሐመድ በነበረበት ጊዜ ወይንም በኋላ ነው፡፡ ይህንንም ጥያቄውን ለማረጋገጥ ምንም ዓይነትም ተዓምራትም አልተሰጡም እንዲሁም ይህንን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ምንም የታወቁ ሰነዶችም የሉም ይህንንም ለማየት (የቁርአንና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊነት የሚለውን ጽሑፍ ተመልከቱ)፡፡ (እንደገና ቼክ ይደረግ)፡፡

ለመጀመሪያዎቹ ቁርአኖች ያሉትን ታሪካዊ ችግሮች አናነሳቸውም ብንልም እንኳን እጅግ ብዙ የሆኑትና ስለ ብዙ የቁርአን ኮፒዎች መኖር የሚናገሩት እጅግ ብዙ ሙስሊማዊ ልማዶች ተጨማሪ ችግርን ያስከትላሉ፡፡ እነዚህም በኡትማን የመሰብሰብ እና የማስታወስ ጊዜ ማለትም በመካከለኛው ሰባት መቶ ዘመን እና ቅራኔ ያላቸው ኮፒዎች በሙሉ እንዲደመሰሱ ተደርጓል፡፡ ስለዚህም አሁን በእጃችን ያለው ቁርአን በመጀመሪያ ተገለጠ ከሚባለው ጋር እንኳን ምን ያህል አንድ እንደሆነ አናውቅም፡፡

ሙስሊሞች መረዳት የሚኖርባቸው ነገር ክርስትያኖች የእግዚአብሔርን ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስን፣ ሁልጊዜ እንደጠበቁት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በሰዎች ነው፤ የጻፉት እነዚህ ሰዎች ግን ሁልጊዜ የነበሩት በመለኮት መገለጥ እና ምሪት ውስጥ የነበረ መሆኑ አስደናቂ አንድነትን ለመጽሐፍ ቅዱስ ሰጥቶታል፤ (2ጴጥሮስ 1.20-21)፡፡

ይሁን እንጂ ቁርአን ስለ እራሱ የሚናገረው ከሰው እጅ ጣልቃ ገብነት ነፃ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆነ ብሎ የመረጠው መንገድ፤ ቃሉን እንዲጽፉ ነቢያትንና ሐዋርያትን በመንፈሱ በመምራት በእነሱ መጠቀምን ነበር፡፡ እነርሱም ቃሉን በታማኝነት እንደተገለጠላቸው አስፍረዋል፤ ስለዚህም ቃሉ ለሰው ልጆች በትክክልና በጥንቃቄ ተላልፏል የተደረገው ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች ለቃሉ ላላቸው ግንዛቤ ኃይልና የመረዳት ችሎታ ጭምር ነው ተላልፎላቸዋል፡፡ ይህንን ቁርአን ሊያደርግ አይችልም ምክንያቱም “እንደሚባለው ሁሉ” ሰዋዊ ነገር በውስጡ የሌለው መሆኑን ስለሚናገር፡፡

ሙስሊሞች ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉውን በቅራኔ የተሞላ ነው በሚሉት ሐሳብ ላይ ሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስሊሞች የራሳቸው ቁርአን ለመጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ስልጣን ምን ለመናገር ይችላሉ?

ቁርዓን ለመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣንን ይሰጣል:

በሙስሊሞች ሁሉ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ቁርአን እራሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣንን ይሰጣል ይህም ከሰባተኛው እስከ ዘጠነኛው መቶ ዓመታት ድረስ እውነታውን በመቀበል ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል የሚከተለውን የቁርዓን ምዕራፍ አስተውሉ፤ ቁርአን 2.136፤ 3.2-3፤ 4.136፤ 5.47፣ 49፣ 50፣ 52፣ 5.68፡፡

የዚህን ሐሳብ ማለትም የብሉይና የሐዲስ ኪዳንን ስልጣን የበለጠ የሚያጠናክር በቁርአን ምዕራፍ 10.94 ላይ እናገኛለን በዚህም ጥቅስ መሰረት ሙስሊሞች የተመከሩት በራሳቸው መጽሐፍ ላይ ጥርጥር ቢያድርባቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመለከቱ ነው፤ ምክሩም፡ ‹ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን› ይህንንም እውነታ እንደማጠናከሪያ ሆኖ እንደገና በቁርአን 21.7 ላይ እንደገና እንደሚከተለው ተደግሟል ‹ከአንተም በፊት ወደነሱ የምናወርድላቸው የኾኑ ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ›፡፡

በመጨረሻም በምዕራፍ 29.46 ላይ ሙስሊሞች የክርስትያኖችን መጽሐፍ ስልጣን በምንም መልኩ መጠየቅ እንደሌለባቸው ተጠይቀዋል፡፡ ‹የመጽሐፉ ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ ከነሱ እነዚያን የበደሉትን ሲቀር በሉም በዚያ ወደኛ በተወረደው ወደናንተም በተወረደው አመንን አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው እኛም ለርሱ ታዛዦች ነን፡፡›

በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ግልጥ ያልሆነ ነገር ምንም ነገር ከሌለ ቁርአን በጥብቅ ቶራንና ወንጌልን ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጡ ትክክለኛና እውነተኛ መገለጦች እንደሆኑ ማረጋገጡ ነው፡፡ ይህም አብሮ የሚሄደው ክርስትያኖችም ከሚያምኑት ነገር ጋር ነው፡፡

በእርግጥ የቀደሙት ቅዱሳን መጻሕፍት ተበክለዋል የሚል ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ በቁርአን ውስጥ የለም እንዲሁም ደግሞ እርስ በእርስም እንደሚቃረኑ የሚናገር ምንም ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ቁርአን የመጨረሻና ሙሉ መገለጥ ከሆነ፤ ሙስሊሞችም እንደሚሉት የቀደሙት ሁሉ መገለጦች መደምደሚያና ማህተምም ከሆነ፤ ከዚያም በእርግጥ የቁርአን ጸሐፊ በቀደሙት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስላሉት መበረዞች በመጥቀስ ማስጠንቀቂያን መስጠት ነበረበት፡፡ ነገር ግን በምንም ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በእርሱ እንደሚቃረን ወይንም በእርግጥም የተበከለ መሆኑን የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሙስሊሞች በምዕራፍ 2.140 መሠረት አይሁዶችና ክርስትያኖች መጽሐፎቻቸውን በርዘዋል በማለት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጥር የሚናገረው (አይሁዶችን በመጥቀስ) ‹... ወይም ኢብራሂም ኢስማኤልም ኢስሐቅም ያዕቁብም ነገዶቹም አይሁዶች ወይም ክርስትያኖች ነበሩ ትላላችሁን? እናንተ ታውቃላችሁን? ወይንስ አላህ? በላቸው እርሱም ዘንድ ከአላህ የኾነችን ምስክርነት ከደበቀ ሰው ይበልጥ በዳይ ማነው? አላህም ከምትሰሩት ሁሉ ዘንጊ አይደለም› ይላል፡፡ ይህም ቁጥር እንኳን ባንድም ቦታ ላይ ክርስትያኖችና አይሁዶች መጽሐፎቻቸውን በክለዋል በማለት የሚናገረው ምንም ነገር የለውም፡፡ የሚናገረውም የሆኑ አይሁዶች መጽሐፎቻቸውን እንደደበቁ ነው ‹ከአላህ ዘንድ የሆነውን ምስክርነታቸውን›፡፡ በሌላ አነጋገር ምስክርነቱ ግን እዚያው ነው ያለው (ስለዚህም የተጠቀሰው የምዕራፍ 2 ቁጥር ሙስሊሞችን የሚናገራቸው ነገር ቢኖር ከዚህ በፊት የመጡትን መጽሐፍት ሙስሊሞች እንዲያከብሩዋቸው ነው)፡፡ ይህም የእነሱ ተከታዮች ምንም ቢደብቁትም እንኳን እንዲያከብሩት ነው፡፡ ይህ ቁጥርም የሚያሳየው ነገር ቢኖር የቀደሙትን መጻሕፍት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ብቻ ነው ምክንያቱም ከበስተኋላ የሚገምተው ነገር ቢኖር የአላህ ምስክርነት በአይሁድ ሕዝብ መካከል ስለመኖሩ ነውና፡፡

እግዚአብሔር ቃሉን አልለወጠም፡

ከዚህም በተጨማሪ የክርስትያኖችም ቅዱሳት መጽሐፍትና የሙስሊሞች ቁርአን የያዙት ዋና ሐሳብ እግዚአብሔር ቃሉን እንደማይለውጥ ነው፡፡ እሱ መገለጡን አይለውጥም (ይህም በቁርአን ውስጥ ከሚገኘው ከአብሮጌሽን ሕግ ወይንም “ከሽረት ሕግ” ውጪ ነው)፡፡ በምዕራፍ 10.64 ላይ እንደሚከተለው እናነባለን ‹... የአላህ ቃላት መለወጥ የላትም ይህ እርሱ ታላቅ እድል ነው› ይላል ይህም እውነታ እንደገና በ6.34 ላይ ‹... የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም ...› በሚል ቃል ተደግሟል እንዲሁም ተመሳሳይ ነገር በምዕራፍ 50.28፣29 ላይ ይገኛል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛም እንደዚሁ የእግዚአብሔር ቃል እንደማይለወጥ የሚያስረዱ እጅግ በርካታ ማስረጃዎችን እናገኛለን ለምሳሌም ያህል ዘዳግም 4.1-2፤ ኢሳያስ 8.20፤ ማቴዎስ 5.17-18፤ 24.35 እና ራዕይ 22.18-20 ላይ ናቸው፡፡

እንግዲህ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስም በቁርአን በተደጋጋሚ የሚገኝ ሐሳብ ከሆነ ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ በማለት የሚናገሩትን ቅራኔ ማግኘት የማይቻል ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡

ይሁን አንጂ ሙስሊሞች አሉ በማለት ስለሚናገሩት ቅራኔ ታዲያ ምን ልናደርግ ይገባናል?

ቅራኔዎች ሲተነተኑ፡

ሙስሊሞች ቅራኔዎች ናቸው በማለት የሚጠቅሷቸውን (የሚጠቆሟቸውን) ስንመለከት የምናስተውለው ብዙዎቹ እነዚህ ቅራኔዎች በጭራሽ ቅራኔዎች እንዳይደሉ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ቅራኔዎች ናቸው በማለት የሚጠቅሷቸውን ሆነው የምናገኛቸው ቃሉ የተገኘበትን ዓውዱን በትክክል ካለመረዳት ወይንም ደግሞ ክፍሉን ኮፒ ካደረጉት ሰዎች ስህተቶች እንደማያልፉ ነው፡፡ ዓውዱን አለመረዳት የሚለው የመጀመሪያው በቀላሉ ሊገለጥ ይቻላል ሁለተኛውና የኮፒ አድራጊዎች ስህተት ግን ትንሽ ተጨማሪ ጥንቃቄ የሞላበት መግለጫ ያስፈልገዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከ17ኛው መቶ እስከ በ5ኛው መቶ ዓመታት ዓመተ ዓለም ድረስ እንደተጻፉ እጅግ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ይህም ደግሞ በዚያን ጊዜ ለመጻፊያ በአገልግሎት ላይ በዋለው በቆዳ እራፊ ላይ እንዲሁም በፓፒረስ ቁራጮችም ላይ እንደነበረ ነው፡፡ እነዚህም በፍጥነት የሚበሰብሱ ስለነበር በየጊዜው ኮፒ ማድረግን የሚጠይቅ ነገር ነበረ፡፡ አሁን እንደምናውቀው የብሉይ ኪዳን ብዙው ክፍል ለ3000 ዓመታት ያህል ኮፒ ይደረግ እንደነበረ ነው፣ ነገር ግን አዲስ ኪዳን ደግሞ ለቀጣቹ 1 400 ዓመታት ያህል ኮፒ ተደርጓል፡፡ ይህም በተለያዩ ቦታዎች ባሉ ማኅበረሰቦች በተለያዩ ምድሮች በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ውስጥ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጣም የሚገርመው ነገር ሁሉም እስከ አሁን በመሠረታዊ ወጥነታቸው ሳይለወጡ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ብዙ የጥንት ቅጂዎች ተገኝተዋል በእነዚህም እኛ ቀደም ያሉ ቅጅዎችን ልንደግፍባቸው ወይንም ልናረጋግጥባቸው እንችላለን፡፡ በእርግጥ እኛ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የቅዱሳት መጽሐፍት ስብስቦች አሉን እነርሱም ጋ በመሄድ እኛ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስን መረጃዎች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ የአዲስ ኪዳንን መረጃዎች በተመለከተ በእጃችን ውስጥ ከ5,300 የሚያክሉ የግሪክ ቅጂዎች አሉን፣ 10,000 የላቲን ቩልጌት መረጃዎች እንዲሁም ቢያንስ 9,330 የሚያክሉ የጥንት ትርጉሞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ከእነርሱ ልንጠቀምባቸው የምንችልባቸው ከ24,000 በላይ የሚሆኑ የአዲስ ኪዳን የጥንት ቅጂዎች ኮፒ ወይንም ክፍሎች አሉን፡፡ ማንኛውንም ሊኖሩ የሚችሉትን ለየት ያሉ ጥቅሶችን በትክክል ልንረዳበት የምንችልበትን እጅግ በጣም ብዙ እድሎችን ይህ የመረጃ እውነታ ይሰጠናል፡፡ የተለየ ክፍል በሚኖርበት ጊዜ እነዚህ ተለይተው ይቀመጡና በግርጌ ማስታዎሻ ላይ ይጠቀሳሉ ይህም የሚደረገው ክፍሉ በሚገኝበት ትክክለኛ ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ ምንም ችግር አለው የሚያስብል ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡

ይሁን እንጂ ክርስትያኖች በቀጥታ የሚቀበሉት ሌላ ነገር ቢኖር በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት የግልባጭ ጽሑፎች ዝግጅት ወቅት “የጸሐፊዎች” ስህተት ሊኖር እንደሚችልም ነው፡፡ ከማንኛውም መጽሐፍ ላይ ገፅ ከገፅ  የሚገለብጥ ማንኛውም ሰው ላይ ሊኖር የሚችልን እያንዳንዷን የብዕር ስህተት ማስወገድ ከማናችንም ችሎታ በላይ ነው፡፡ ይህም መንፈሳዊም ይሁን ስጋዊም (ዓለማዊ) እውነተኛ የሆነ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች (ማኑስክሪፕትስ ወይንም በተሻለ አጠራር ኦቶግራፍስ) እያንዳንዱ መጽሐፍ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀጥታ በመገለጥ የተሰጠ በመሆኑ ከማናቸውም ስህተት የፀዳ ነው፡፡ (ምንም ስህተት የሚባል ነገር የለበትም)፡፡ እነዚያ የመጀመሪያዎቹ በእርግጥም ከጥንታዊነታቸው ከተጻፉባቸው ነገሮች አኳያ ሁሉ ከጊዜውም እርዝመት ቀጥለው አልተገኙም፡፡ (በአሁኑ ጊዜ የሉም)፡፡

ቃሉን ለመጻፍ ሃላፊነት የነበራቸው ግለሰቦች (ጸሐፍት ወይንም ቀጂዎች) ሁለት ዓይነት ስህተቶችን ለማድረግ የሚችሉ ነበሩ፣ እነዚህም በማኑስክሪፕት ጥናት ትንተና ላይ በተሰማሩ ሊቃውንት በጣም የታወቁና በሚገባም የተመዘገቡ ናቸው፡፡ አንደኛው መደበኛ ስሞችን ፊዳለት (በተለይም ያልተመለመዱ የውጭ ስሞችን) በተመለከተ የሚኖረው ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ ቁጥሮችን በተመለከተ የነበረው ነው፡፡ በአብዛኛው እንደዚህ ዓይነት ስተቶች የመኖራቸው እውነታ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የጸሐፊዎች ስህተት ነው የሚለውን ነገር ታማኝነትን ያስገኝለታል፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ በቅራኔ የነበሩ ቢሆኑ ኖሮ እኛ ልንመለከት የምንችለው ነገር፤ በታሪኮቹ ይዘት ውስጥ እራሱ ማስረጃዎች እንደሚኖሩ ነው፡፡

እዚህ ላይ ማንኛውም ሰው ማስታዎስ የሚገባው በጣም ጠቃሚ የሆነው ነገር፤ ልዩነት ነው ተብሎ የቀረበና የመጣ ማንኛውም የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በፍፁም እንዳልቀየረው ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ ረገድ ላይ የቃሉ ጸሐፊ መንፈስ ቅዱስ የጽሑፉን መተላለፍ በተመለከተ ከስህተት ይጋርድ፤ ይቆጣጠርና በአጠቃላይ ሂደቱን ሁሉ ይጠብቅ እንደነበረ መመልከት እንችላለን፡፡

እግዚአብሔር በየትኛውም ቦታ ላይ ቅዱሳት መጽሐፍት ሲቀዱና ሲተላለፉ ምንም ስህተት አይኖርም ብሎ ቃልን ስላልገባ፣ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ልናረጋግጠው የምንችለው ነገር በእግዚአብሔር መንፈስ ቀጥታ የመጡት የመጀመሪያዎቹ ጽሐፎች ኦቶግራፍስ ጽሑፎች ብቻ ናቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ምንም ስህተት ሊኖርባቸው አይችልም የሚለውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በጽሐፉ መተላለፍ ውስጥ ገብተው የነበሩ ማንኛቸውንም ጥቃቅን ስህተቶችን ነቅሶ ለማውጣት የሚያስችለንን የቴክስቹዋል (የጽሑፍ) ጥናታዊ ትንተና በቀጣይነት ማካሄድ የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቴክስቹዋል ትንተና ሳይንሳዊ ጥናት ውሳኔ ወይንም ብይን የሚመያለክተው ነገር የሒብሩውና የግሪኩ ጽሑፎች በሚገባ ተጠብቀው እንደቆዩ ነው፡፡ ስለዚህም እኛ አሁን ከዌስት ሚኒስተር ኮንፌሽን ጋር በብዙ ማስረጃ የምናረጋግጠው በዚህ ጉዳይ ላይ የተከሰተውን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ስራ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን በማንኛውም ሁኔታና መንገድ እንዳልተበከለና አሁን በእጃችን ያሉት ቅጂዎች ሙሉ ለሙሉ ከስህተት የፀዱ መሆናቸውን ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ምንም ዓይነት ትርጉም ስራ ፍፁም አይደለምና ወይንም ሊሆንም አይችልምና ማንኛውም የትርጉም ስራ ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ተጨማሪ እርምጃ ፈቀቅ ያለ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ነገር ግን የቋንቋ ሳይንስ ውሳኔ እንደሚያሳየው ከሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢያንስ እጅግ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ አገልግለዋል፡፡ በእነዚህም ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ግሩም እና ብዙ በሆኑ ትርጉሞች ውስጥ ትክክለኛው የእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል በእጃቸው መኖሩን ለመጠራጠርና በዚህም የተነሳ ለማመንታት ምንም ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ በእርግጥ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ የቀረበውን ዋና ጉዳይ በተመለከተ እንዲሁም በቃሉ ውስጥና በቃሉ ከመንፈስ ቅዱስ ከምናገኘው ተደጋጋሚ ምስክርነት፣ እውነተኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንባቢው “ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል” 2ጢሞቴዎስ 3.15 የሚለውን ትርጉም እውነታ እንዳይረዳ ከመርዳት አያስቀሩትም፡፡

ይህንን በአዕምሯችን ይዘን አሁን እኛ ለመመልከት የምንሄደው በሻቢር አላይ ጽሑፍ ላይ የተሰነዘረውን ምሳሌ ነው ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በላይ የተረጋገጠውን ሃሳብ የሚያሟላ ወይንም የማያሟላ መሆኑን ለመፈተን ለመመልከት እንሄዳለን፡፡

እነዚህን የሙስሊሞች ሊቃውንትን ተግዳሮቶች በመመለስ ላይ እያለን ለአራቶቻችን ጸሐፊዎች ግልፅ የሆነልን ነገር ሻቢር አላይ እጅግ ብዙ ስህተቶችን እንደሰራ ነው፡፡ እነዚህም የእርሱ ስህተቶች አውዶችን ቢመለከት ኖሮ በቀላሉ የሚታረሙ ነበሩ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አውዱን በማንበብ ብቻ ግልፅ የሚሆኑትን ቅራኔዎችን የሚመስሉ ነገሮችን በጣም ብዙ ሙስሊሞች በአጠቃላይ ለመፈለግ ለምን እንደሚናፍቁ ይህ ሐሳብን ይሰጠናል፡፡ በተቃራኒው ቁርአንን በምንመለከትበት ጊዜ ግን ሁኔታ በሁኔታው በጣም እንደነቃለን ምክንያቱም ቁርአን አውድን ለመመልከት የምንችልበት በጣም ጥቂት አውድ ብቻ አለውና፡፡ ቁርአን በጣም ጥቂት ትረካ ብቻ ነው ያለው፡፡ እንዲሁም ደግሞ አንቀፆች እርስ በእርስ ምንም የሚያገናኝ ሐሳብ የሌላቸውን ሌሎች አንቀፆችን ያስገባሉ፡፡ በሌላም ምዕራፍ ላይ ደግሞ ተመሳሳይ ሐሳብ እንደገና ይነሳል እንዲሁም በሌላ ቦታ ደግሞ ይደገማል ይህም በተለያየ መንገዶችና አንዳንድ ጊዜም በተቃረነ ሐሳብ ዙሪያ ላይም ነው (ለምሳሌም በቁርአን ምዕራፍ 21.51-59ና በ6.74-83፣ እንዲሁም በ19.41-49 አብርሃምንና የጣዖት አምልኮን በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦችን እናነባለን)፡፡ ለአዕምሮም ግልፅ የሆነውም ሙስሊሞች በቁርአናቸው ላይ የአንድን ክፍል ከሌላ ክፍል አውድ ላይ መውሰድ እንዳልቻሉ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ በቁርአን የሚያደርጉትን ዓይነት ተመሳሳይ ነገር አለማድረጋቸው ምን አስደናቂ ነገር ነው!

በሻቢር አላይ “101 ግልፅ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅራኔዎች” ትንሽ መጽሐፍ ገፅ ሁለት ላይ የተጠቀሰው የሚከተለው ዓረፍተ ነገር ነው፡ “ፈቃድ ተሰጥቷል! እባካችሁ ይህችን ትንሽ መጽሐፍ እያባዛችሁ እውነትን አሰራጩ”፡፡

እኛ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊዎች የአቶ ሻቢር አላይን ጥያቄ ለማሟላት ደስተኞች ሆነናል፡፡ ምንም እንኳን እኛ የእርሱን ቃላት እንዳለ ያልገለበጥን ብንሆንም እርሱ ቅራኔዎች ናቸው በማለት በትንሽ መጽሐፉ ውስጥ የሚላቸውን ገልብጠን ምላሽን ሰጥተንባቸዋል፡፡ ስለዚህም በእነዚህ ተቃውሞዎች ውስጥ እኛ የምንሰራው ሻቢር የጠየቀውን ነገር ማለትም እውነትን ማሰራጨትን ነው፡፡ በዚህም የመጽሐፍ ቅዱስን ጥብቅና እውነተኛ መሰረት በማሳየት እርሱ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን አንባቢዎች እንዲረዱ ነው፡፡

ስለዚህም በዚህ የእኛ የተቃውሞ መልስ ውስጥ የአቶ ሻቢር አላይን ቃላት እባካችሁ መዝኗቸው፡፡

እንደምትመለከቱትም ብዙ ጥያቄዎች ከአንድ በላይ መልሶች አሏቸው፡፡ ይህም የተደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ ቴክስቶች ውስጥ አሉ የሚባሉትን ችግሮች የመመልከት የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ ለማሳየት ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ሙስሊሞች ሁልጊዜ ከሚያነሷቸው ጥቄዎች ውስጥ ዋናዎቹ ያነጣጠሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ በሚሏቸው ቅራኔዎች ላይ ነው፡፡ እነዚህንም ጥቄዎች ለብዙ ክርስትያኖች ያቀርባሉ፣ ከዚህ በላይ በቀረበው ጽሑፍ ላይ ግልፅ እንደሆነው ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ሁለት መሠረታዊ የግንዛቤ ችግሮች አሉባቸው፡

አንደኛ፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ እርሱን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ እራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ሎጂካል የሆኑ መልሶች እንዳሉት አለማወቅም ለማወቅም አለመፈለግ ናቸው፡፡

ሁለተኛ፡ የራሳቸው መጽሐፍ ቁርአን፤ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚናገረውን ነገር በትክክል አለመረዳትም አለበት፡፡ ሙስሊሞች አሁን የሚናገሩትን ነገር ቁርአን አይናገርም፡፡ ቁርአን ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ከበሬታ እንዳለው ከዚህ በላይ ያለው ጽሑፍ ያሳየናል፡፡ ታዲያ ሙስሊሞች  ቁርአን ከሚናገረው ውጭ ለምን መሄድ አስፈለጋቸው? ቁርአንን በሌላ ዓይነት መንገድ ለመደገፍ ያለው አማራጭ ይህ ብቻ ነው በማለት አስበው ይሆንን?

ለማንኛውም ብዙዎች ሙስሊሞች በተለያየ ጊዜ ለሚያነሷቸው አሉ የሚባሉ ቅራኔዎች የቀረቡትን መልሶች አንባቢዎች በተከታታይ ቢከተሏቸው ለጥቄዎቻቸው መሰረታዊ የሆነ ምላሽን ማግኘት ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚነቀፍ ነገር እንደሌለውና ለሕይወት እንቆቅልሾች ሁሉ መፍትሄ ያለው መጽሐፍ እንደሆነ ማስተዋል እንደሚችሉ እናምናለን፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፣ እኛ ከማሳሰብ የማናቋርጠው ነገር የሃይማኖት ጉዳይ የሕይወት ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ክርስትና ቡድንን መቀላቀል ወይንም የባህል ወይንም የትውልድ እምነትን መጠበቅ ማለት አይደለም፡፡ ክርስትና በእውነት ላይ ማለትም በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲሁም በሕይወት ቃል ላይ መመስረት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የእውነተኛው ክርስትና መሠረት ለሰው ሕይወት መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስን በመስጠት ብቸኛ መሰረት ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንባቢዎች እንዲያስቡባቸው እናቀርባለን፡፡ ሕይወት ምንድነው? ለምን ሰው ሆነን ተፈጠርን? የሰው ልጅ ሁሉ መሰረታዊ ችግሩ ምንድነው? ለዚያስ መልስ የሚያገኘው ከየት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ የሰው ልጅ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ድርሻው ምንድነው? እርሱስ ለሰጠው እውነተኛ መፍትሄ ምላሻችን ምን መሆን አለበት? ወ.ዘተ፤ መልሶቻቸው በትክክል የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህም እውነትን ለማወቅ ጉጉት ያላችሁና እውነትንም የተጠማችሁ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በተከታታይ እንድታነቡ በእግዚአብሔር ፍቅር እንጠይቃችኋለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔርም በምህረቱና በፀጋው ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: "101 Cleared-up Contradictions in the Bible"

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ