በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት - የእስላም ግራ መጋባት!

Derik Adams

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

አይሁዶችና ክርስትያኖችን በመጥቀስ አላህ ተናገረው ስለተባለው ነገር በቁርአን ምዕራፍ 4.157 ላይ እናገኛለን፡፡

‹እኛ የአላህን መልእክተኛ የመርየምን ልጅ አለመሲሕን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው) አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡›

በክርስቶስ ስቅለት ዙሪያ አላህ የሚናገረው ነገር ለእራሱ ተከታዮች ማለትም ለሙስሊሞችና ለዑማው (ለሙስሊም አገርና ለማህበረሰቡ) ወጥነት ያለውና ምንም ጥርጥር የማያስከትል መሆኑንና አለመሆኑን ለማየት ቆረጥኩኝ፡፡ (ይህም በስቅለት ዙሪያ በትክክል የተከናወነው ምን እንደሆነ አላህ ይናገር እንደሆነ ለማየት ነው)፡፡ የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ፣ አላህ፣ ለሚከተለው ለሙስሊሙ ማህበረ ሰብ (ለዑማው) ያለምንም ጥርጥርና ግራ መጋባት ግልፅ መልእክት ከሌለው፣ አይሁዶችንና ክርስትያኖችን እኩል የሚነቅፈው ለምንድነው?

ስለዚህም በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በትክክል ስለሆነው ነገር እስላሞች የሚሰጡትን ሐሳቦች አሁን እንመልከት፡፡ (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የጌታን ስቅለት በተመለከተ በሙስሊም ሊቃውንት የተሰጡ አራት ፅንሰ ሐሳቦች ወይንም ቲዎሪዎች ይገኛሉ)፡፡ 

አንደኛ፡- የምትክ ፅንሰ ሐሳብ ወይንም The Substitution Theory

ይህ ፅንሰ ሐሳብ እጅግ ብዙ በሆኑ የሙስሊም ተንታኞች ተደጋፊነት ያለው ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ሦስቱን ዋና ትንተናዎች ከዚህ በታች እንመለከታለን፡፡

ሀ. የአቡ አል-ፊዳ ትንተና፡- Abu Al-Fida, 'Imad Ad-Din Isma'il bin 'Umar bin Kathir Al-Qurashi Al-Busrawi (1301-1373), ታዋቂ የሆነው የቁርአን ተንታኝ ሲሆን ቁርአን 4.157 በተመለከተ የሚከተለውን ትንተና ሰጥቷል፡፡

አይሁዶችም እንደሚከተለው ተናገሩ፤ ‹እኛ የአላህን መልእክተኛ የመርየምን ልጅ አለመሲሕን ገደልን›፣ ማለትም የአላህ መልእክተኛ ነኝ በማለት የተናገረውን ሰው ገደልነው ማለት ነው፡፡ አይሁዶቹ እነዚህን ቃላት የተናገሩት በቀልድ እና በማሾፍ ነው፣ ይህም የብዙ ጣዖታት አምላኪዎቹ እንደሚናገሩት ነው፡፡

(ኦ እናንተ ቁርአን ከላይ የወረደላችሁ! በእርግጥ እናንተ እብድ ሰው ናችሁ)፡፡ አላህ ዒሳን በማስረጃና በምሪት በላከው ጊዜ አይሁዶች፣ አላህ ይርገማቸውና፣ ተቆጡ (ተናደዱ)፣ ስቃይና ቅጣት በእነሱ ላይ ይሁን፣ እነሱ በእሱ ላይ ቀኑበት ምክንያቱም ነቢይነቱ በግልጥ ተዓምራት ነበርና፣ እውራንን በማብራት፣ ለምፃሞችን በማንፃት የሞቱትን እንደገና ወደ ሕይወት በመመለስ እንደ አላህ ፈቃድ ነበርና፡፡ እንዲሁም እሱ ከሸክላ ጭቃ ወፍን ሰርቶ ሲነፋባት በአላህ ፈቃድ ወፍ ሆና በርራለች፡፡ ዒሳ ሌሎችንም ተዓምራቶችን አድርጓል ነገር ግን አይሁዶቹ ክደውታል አሹፈውበታል እንዲሁም እሱን ለመጉዳት የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ የአላህ ነቢይ ዒሳ (ሰላም በእሱ ላይ ይሁን) በአንዲት የተወሰነች ከተማ ሊኖር አልቻለም ነበር ስለዚህም ከእናቱ ጋር ከከተማ ወደ ሌላ ከተማ መዘዋወር ነበረበት፡፡ ሆኖም አይሁዶች በዚህም ስላልረኩ በዚያን ጊዜ ከዋክብትን ያመልክ ወደነበረው ግሪካዊ (የብዙ ጣዖታት አምላኪ) ፖሊቲስት ወደሆነው የደማስቆ ንጉስ ሄዱ፡፡ እነሱም ለእሱ ሄደው ቤት - አል መቅደስ በተባለው ቦታ ላይ አንድ ሰው እንደነበረና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ እያሳሳተ እና እየከፋፈለ በንጉሱ ሕዝብ ላይ አለመረጋጋትን እንዳስከተለ ነገሩት፡፡ ንጉሱም ተናደደና ዓመፀኛው እና እረፍትን የነሳው መሪ ተይዞ እንዲሰቀል፣ በእራሱም ላይ የእሾህ አክሊል እንዲደረግበት የሚል ትዕዛዝ የያዘ ደብዳቤን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፡፡ በኢየሩሳሌም ያለው የንጉሱ ተወካይ ይህንን ደብዳቤ እንዳገኘ ከአንዳንድ አይሁዶች ጋር በመሆን በኢየሩሳሌም ዒሳ ወደሚኖርበት ቤት ሄደ፣ እሱም ከአስራ ሁለቱ ወይንም ከአስራ ሦስቱ ወይንም ከአስራ ሰባቱ ተከታዮቹ ጋር ነበር፡፡ ያም ቀን አርብ ነበር ማታም ነበር፡፡ ዒሳንም በቤት ውስጥ እንዳለ ከበቡት እሱም ወዲያውኑ ወደ ቤት ውስጥ እንደሚመጡ፣ ወዲያው ወይንም ቆይቶ ቤቱን ለቆ መሄድ እንዳለበት ሲሰማው፣ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ተናገራቸው፡- ‹ማነው እኔን ለመምሰል ፈቃደኛ የሚሆነው እሱ ከእኔ ጋር በመንግስተ ሰማይ (በገነት) ይሆናልና?  በማለት ጠየቀ›፡፡ ከእነሱም ወጣቱ ፈቃደኛ ሆነ ነገር ግን ዒሳ እሱ በጣም ወጣት መሆኑን አሰበ፡፡ ጥያቄውንም ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጠየቀ በእያንዳንዱም ጊዜ ውስጥ ወጣቱ ሰው ፈቃደኛ ሆነ ስለዚህም ይህ የወጣቱ ፈቃደኛነት ዒሳን እንደሚከተለው እንዲናገር አስደረገው፡- ‹ደህና አንተ ያንን ሰው ትሆናለህ›፡፡ አላህም ያንን ወጣት ሰው ልክ ዒሳን እንዲመስል አደረገው፣ የቤቱም ጣሪያ ክፍት እየሆነ እያለ ዒሳ እንዲያንቀላፋ ተደረገና ወደ ሰማይ ተወሰደ በእንቅልፉም ውስጥ እያለ፣ አላህ የሚከተለውን ተናገረው፡-

‹አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ) ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ› 3.55 (ይህ የጥቅስ ማገናዘቢያ የተጨመረው በአዘጋጆቹ ነው)፡፡ ዒሳም ወደ ሰማይ በተወሰደ ጊዜ በቤት ውስጥ የነበሩት እነዚያ ወደ ውጭ ወጡ፡፡ ቤቱንም የከበቡት ሰዎች ዒሳን የመሰለውን ሰውየ ባዩት ጊዜ ዒሳ እንደሆነ አሰቡ፡፡ ስለዚህም እሱን በምሽት ወሰዱት ሰቀሉትም በእራሱም ላይ የእሾህን አክሊል አደረጉበት፡፡ አይሁዶችም ዒሳን ገደልነው በማለት ጉራቸውን መንፋት ጀመሩ፣ አንዳንድ ክርስትያኖችም የእነሱን አባባል ተቀበሉት ይህም በድንቁርናቸውና ማስተዋልን በማጣታቸው ነው፡፡ ከዒሳ ጋር በቤት ውስጥ የነበሩት ግን ወደ ሰማይ የማረጉን እውነታ መስክረዋል አንዳንዶቹም ዒሳን አይሁዶቹ ሰቅለው እንደገደሉት አስበዋል፡፡ እነሱም የተናገሩት ነገር ማርያም እራሷ ተሰቅሎ በተገደለው ሰው እሬሳ አጠገብ ተቀምጣ ስታለቅስ የሞተው ሰው እሬሳ ከእርሷ ጋር ተነጋግሯል በማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከአላህ ነው፣ ይህም ባሪያዎቹን ይፈትነበት ዘንድ፣ ከእሱ ሁሉን አዋቂነት የተነሳ ነው፡፡ አላህም ይህንን ጉዳይ መልክተኛ አድርጎ በላከው ሰው በኩል በከበረው ቁራኑ ውስጥ ገልጦታል፡፡ እሱንም አላህ በግልጥ ተዓምራትና እንዲሁም ወደር በሌለው ማስረጃዎች አረጋግጦታል፡፡ አላህ እጅግ በጣም እውነተኛ ነው እሱም የዓለማት ሁሉ ጌታና ምስጢራትን ሁሉ አዋቂ ነው፣ በልብ ውስጥ የተደበቀውን በሰማይም በምድርም ሁሉ የተደበቀውን ነገር ሁሉ እሱ ያውቃል፡፡ የሆነውን የሚሆነውን ከእሱ ዘንድ ከተወሰነ መሆን የሚገባውን ነገር ሁሉ እሱ ያውቃል፣ እሱም የተናገረው፡-

‹አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣› በማለት ነው፣ ይህንንም የተናገረው አይሁዶች ዒሳን የመሰላቸውን ሰው በተመለከተ ሲናገር ነው፡፡ ለዚህ ነው ከዚህ በኋላ አላህ እንደሚከተለው የተናገረው፡- ‹በዚህ ነገር የሚለያዩት እነዚያ በጥርጥር የተሞሉ ናቸው፡፡ እነሱም እርግጠኛ የሆነ እውቀት የላቸውም እነሱም የሚከተሉት ነገር ጥርጥርን ብቻ ነው›፡፡ ይህንንም የተናገረው ዒሳን ገደልን በማለት ለተናገሩት አይሁዶችና የእነሱንም አባባል ተቀብለው ላመኑት ክርስትያኖች ነው፡፡ በእርግጥ እነሱ ሁሉም በተምታታ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፣ በመምታታትና በመጠራጠር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህም አላህ እንደሚከተለው ተናገረ፡-

‹በእርግጥ እርሱን አልገደሉትም› ማለትም እነሱ የገደሉት ዒሳ ለመሆኑ እርግጠኞች አይደሉም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን በተመለከተ እነሱ በጥርጥርና በመዋዠቅ ውስጥ ናቸው ማለት ነው፡፡

‹ነገር ግን አላህ ወደ እራሱ አንስቶታል፡ አላህም ሁልጊዜ ኃይለኛ ነው› ማለትም እሱ ሁሉን ቻይ እና በምንም ጊዜ ውስጥ ቢሆን እሱ ደካማ ሆኖ አያውቅም በእሱም ዘንድ መጠጊያ ያደረጉት እነዚያ በምንም መንገድ አያፍሩም፡፡

(ሁሉን አዋቂ) በፍጥረቱ ውስጥ በሚወስነው እና በሚያደርገው ነገር ሁሉ አላህ አዋቂ ነው፡፡ በእርግጥ አላህ፣ ግልጥ የሆነ ጥበብ፣ ተወዳዳሪ የሌለውና እጅግ በጣም የከበረ ስልጣን ነው፡፡ ኢብን አቢ ሃቲም እንደዘገበውና ኢብን አባስ እንዳለው ‹አላህ ዒሳን ወደ ሰማይ ከመውሰዱ በፊት ዒሳ በቤት ውስጥ ወደነበሩት አስራ ሁለቱ ተከታዮቹ ሄደ፡፡ እሱም እንደ ደረሰ ፀጉሩ ውሃን ያንጠባጥብ ነበር እሱም የሚከተለውን ተናገረ፡ ‹ከእናንተ መካከል በእኔ ካመኑ በኋላ አስራ ሁለት ጊዜ የሚክዱኝ አሉ አለ፣ ደግሞም እንደገና ‹መልኩ የአኔን መልክ እንዲመስል፣ በእኔም ምትክ እንዲሞት ከእናንተ መካከል ፈቃደኛ የሚሆን ማነው? ፈቃደኛ የሆነውም በገነት ከእኔ ጋር ይሆናል አለ፡፡ ከእነሱም መካከል እጅግ በጣም ወጣት የሆነው ፈቃደኛ ሆነ ‹ዒሳም እሱን እንዲቀመጥ ጠየቀው›፣ ‹ዒሳም እንደገና ፈቃደኛ ለሚሆን ሰው ጥያቄን አቀረበ›፣ ወጣቱ ሰውም እንደገና ፈቃደኛነቱን መግለጡን ቀጠለ፣ ዒሳም እንደገና እንዲቀመጥ ጠየቀው፣ ከዚያም ወጣቱ ሰው እንደገና ፈቃደኛነቱን ገለጠ ከዚያም ዒሳ ‹ያ ሰው አንተ ትሆናለህ› በማለት ተናገረ፣ ከዚያም በቤቱ ጣሪያ ክፍተት ዒሳ ወደ ሰማይ እየተወሰደ እያለ የዒሳ ምስል በእሱ ላይ ሆነበት፡፡ አይሁድም ዒሳን ለመያዝ ወደ ቤቱ ውስጥ በመጡ ጊዜ ወጣቱን ሰው አገኙትና ሰቀሉት፡፡ ከዒሳ ተከታዮችም አንዳንዶቹ በእሱ ካመኑ በኋላ እንደገና ለአስራሁለት ጊዜም ያህል በእርሱ አላመኑም ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ እነሱ ወደ ሦስት ቡድን ተከፋፈሉ ክፍፍሉም፡-

አንደኛ፡- ያአ - ኩቢያ (ያዕቆባውያን)፣ የሚባሉት ሲሆኑ እነሱም የሚያምኑት ‹አላህ እስከፈቀደ ድረስ ከእኛ ጋር ኖረ ከዚያም ወደ ሰማይ ተወሰደ› በማለት ነው፡፡

ሁለተኛ፡- አን - ናስቱሪያህ (ኔስቶራውያን)፣ የሚባሉት ሲሆኑ እነሱም የሚያምኑት ‹የአላህ ልጅ ከእኛ ጋር አላህ እስከፈቀደ ድረስ ነበረ፣ ከዚያ አላህ ወደ እራሱ እርሱን ወሰደው› በማለት ነው፡፡

ሦስተኛ፡- ሙስሊሞች የሚባሉት ሲሆኑ፣ እነሱም የሚያምኑት ‹የአላህ ባሪያና መልእክተኛ አላህ እስከ ፈቀደ ድረስ ከእኛ ጋር ኖሮ ነበር ከዚያም አላህ ወደ እራሱ ወሰደው› በማለት ነው፡፡

ከዘህ በላይ ያሉትና ሁለቱ አላህን የማያምኑት (ያዕቆባውያንና ኔስቶራውያን ለመጥቀስ ነው) ቡድኖች በሙስሊሞች ላይ ተባበሩና ሙስሊሞችን በሙሉ ገደሏቸው፡፡ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ አላህ መልእክተኛውን መሐመድን እስከላከበት ጊዜ ድረስ እስልምና ተሸፍኖ ነው የኖረው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገርም እስከ ኢብን አባስ፣ እና አን-ናሳይ ትረካ ድረስ ታማኚነት ያለው ነው፡፡ ይህም ከአቡ ሙዊያህ ተቀብሎ በዘገበው በአቡ ኩራይብ ተነግሯል፡፡ ብዙዎች ከ-ሳላፍ የተናገሩት ነገር ‹ከተከታዮቹ መካከል ዒሳን ለመምሰል እና በምትኩም እንዲሞት ዒሳ ፈቃደኛ የሆነን ሰው እንደጠየቀና እሱም ከእሱ ጋር በገነት ተከታዩ እንደሚሆን እንደተናገረ ገልጠዋል፡፡› (Tafsir Ibn Kathir on 4:157

ለ. የአል-ጃላላይን ትንተና፡- ቁርአንን ለማጥናት በጣም ጠቃሚ የሆነው ታፍሲር Tafsir al-Jalalayn የሚባለው ነው፡፡ በሁለቱ ጃላሎች ማለትም በ Jalal al-Din al-Mahalli (d. 864 ah / 1459 ce) and his pupil Jalal al-Din al-Suyuti (d. 911 ah / 1505 ce), የተቀናበረው ጃላላይን አንድ መጽሐፍ በመሆኑና በቀላሉ ሊገባ ተደርጎ የተሰራ የቁርአን ትንተና ስለሆነ በጣም ተቀባይነትና ታዋቂነት ያለው ነው፡፡ ታፍሲር አል-ጃላላይን ለመጀመሪያም ጊዜ በጥራት እና ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ በትክክል እና በሚነበብ መልኩ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በDr. Feras Hamza. ነው፡፡

ስለዚህም አል-ጃላላይን ከቁርአን 4.157 ላይ የሚከተለውን ነገር ያርባል፡-

እነሱም በትዕቢት ለሚናገሩት፣ ‹እኛ የአላህን መልእክተኛ የመርየምን ልጅ አለመሲሕን ገደልን በማለታቸው› እነሱም እንደተናገሩት፣ በሌላም አነጋገር ለእነዚህ ነገሮች ሁሉ እነሱን ቀጣናቸው፡፡ እግዚአብሔር ክቡር ይሁን፣ እሱም የተናገረው ዒሳን ገደልነው ማለታቸውን በመቃወም ነው፡፡ ነገር ግን እነሱ ዒሳን አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ነገር ግን እሱ በነሱ የተገደለው ሰው የእነሱው ዘመድ ነው (አይሁዳዊ ነው) እሱም የኢየሱስን መልክ እንዲመስል ተደርጎ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር በእሱ ላይ የኢየሱስን ምስል አድርጎበት ነበር፣ ስለዚህም እነሱ ያሰቡት እርሱ ዒሳ ነው ብለው ነበር፡፡ እነዚያም በዚህ ጉዳይ ላይ ያልተስማሙት ማለትም ኢየሱስን በተመለከተ በእርግጥ በእርሱ መገደል ላይ በጥርጥር ውስጥ ናቸው፣ ምክንያቱም ከእነሱ አንዳንዶቹ እንደሚከተለው ብለዋልና የተገደለውን ሰው በተመለከቱበት ወቅት ፊቱ የኢየሱስን መስሎ ነበር ነገር ግን አካሉ ግን የሌላ ሰው ነበር ስለዚህም አንዳንዶች እሱ ኢየሱስ አይደለም ሲሉ ሌሎች ደግሞ አይደለም ይህ ኢየሱስ ነው ይሉ ነበር፡፡ ስለዚህም የእሱን መገደል በተመለከተ እነሱ ምንም እውቀት የላቸውም ነበር፤ እነሱም ያላቸው ግምት ብቻ ነበር፡፡ በሌላም አነጋገር እነሱ ይከተሉ የነበረው ነገር ‹ግምትን ብቻ ነበር፣ ያም እነሱ የገመቱት ነገር ነበር› እነሱም እርሱን በእርግጥ አልገደሉትም፡፡ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡› (Tafsir Al Jalalayn on 4:157፡፡

ሐ. የኢብን አባስ ትንተና፡- ሌላው ታፍሲር ደግሞ Tafsir Ibn 'Abbas ነው፡፡ በዚህ ታፍሲር ውስጥ የቀረበው ነገር በAbdullah Ibn Abbas (d. 68/687) and to Muhammad ibn Ya‘qub al-Firuzabadi (d. 817/1414), ከቀረበው የተለየ ነው፣ ይህ የTanwîr al-Miqbâs ታፍሲር በቁራን ትንተና እድገት አጠቃላይ ሁኔታ ግንዛቤን ለማግኘት ወሳኝ ከሆኑት ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የጸሐፊው ማንነት እርግጠኛ ካለመሆኑና አወዛጋቢ ከሆነው የእስራኤላውያን ትረካው በስተቀር፣ Tanwîr al-Miqbâs በእስላሞች፣ በአይሁዶችና በክርስትያኖች መካከል ስለነበረው የእስላማዊ ሐሳቦች ስርጭትና የሐሳብ መለዋወጥ ዙሪያ ላይ በእስላሞች መካከል ጽሑፉ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ መረዳቶችን ይሰጠናል፡፡ ይህም በእስላማዊ ትንተና መሰረታዊ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ ስለዚህም በቁርአን 4.157 ላይ የሚከተለውን እናገኛለን፡- Ibn 'Abbas on 4:157፡-

‹እኛ የአላህን መልእክተኛ የመርየምን ልጅ አለመሲሕን ገደልን በማለታቸው› አላህ የእነሱን ሰው ታቲያኖስን አጠፋው፡፡ ‹አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣› አላህም ታቲያኖስ ኢየሱስን እንዲመስል አደረገው ስለዚህም በእሱ ምትክ እሱን (ታቲያኖስን) ገደሉት፡፡ ‹እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት› በእርሱ መገደል በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ‹ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም› በእርግጥም አልገደሉትም፡፡› በእርግጥም እሱን አልገደሉትም፡፡ (Tafsir Ibn 'Abbas on 4:157፡፡

በሳም ሸሞን የተጻፈው The Quran, Bible Preservation and the Crucifixionhttp: በሚለው ጽሑፍ ውስጥ በ www.answering-islam.org/Shamoun/preserved-crucifixion.htm (ለእስላም መመለስ የእንግሊዝኛው ድረ ገፅ ላይ) እንደሰፈረው ኢየሱስ ክርስቶስን ተክቶት የሞተው ማን ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ በሙስሊሞች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት አለ፡፡ የሚከተለውም ነጥብ ይህንን በግልፅ ያሳየናል፡፡

‹እግዚአብሔር አንድ ሰው ኢየሱስን እንዲመስል አደረገው እሱም በክርስቶስ ምትክ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ይህም የሚታወቀው ‹የምትክነት substitution theory በመባል ነው› ይሁን እንጂ ይህ ትርጉም አጅግ በጣም ብዙ በሆኑ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡ በመጀመሪያም በእርግጥ ክርስቶስ ኢየሱስን እንዲመስል የተደረገው ሰው ማነው? የሚለው ነው፡፡ ሙስሊሞች ይህንን በተመለከተ ወጥነት የላቸውም ስለዚህም ምትክ ሆኖ ስለሞተው ሰው የሚከተሉትን ነገሮች ይናገራሉ፡-

ሀ. አንዳንዶች ይሁዳ ነው ይላሉ፡፡

ለ. ሌሎች ደግሞ ከኢየሱስ ደቀመዛምርት አንዱ ነው ይላሉ

ሐ. አሁንም ሌሎች ደግሞ ታቲያኖስ የተባለው የሮም ወታደር ነው ይላሉ፡፡

ሁለተኛ፡- የመሳት-ፅንሰ ሐሳብ (እራስን የመሳት) The Swoon Theory

ኢየሱስ ተሰቅሎ ነበር ነገር ግን አልሞተም፡፡ በመስቀል ላይ እራሱን ስቶ፣ ቆይቶ ወደ ነፍሱ ተመልሷል፡፡

ምንም እንኳን ይህ የመሳት-ፅንሰ ሐሳብ ወይንም (የሱዉን ቲዎሪ) በአብዛኛው የእስላማዊ የኑፋቄ ትምህርት አራማጆች ናቸው በሚባሉት በአህመዲያዎች እንዲሁም በእስላም አገሮች ተቀባይነት ያለው ቢሆንም፣ ብዙዎቹ ጤናማ የሱኒ እምነት ተከታዮችም ይህንን ቲዎሪ ተቀብለውታል፡፡ በጣም ታዋቂው የሱኒ አስተማሪ አህመድ ዲዳትም ለክርክር ዓላማው ሲል ይህንን የመሳት-ፅንሰ ሐሳብ ተቀብሎታል፡፡  

ይህንን ቲዎሪ ለመቀበል ከወሰኑት ሰዎች መካከል አክባራሊ መሐራሊም ይገኝበታል፡፡ መሐራሊ የምትክነት ቲዎሪ የተባለውን እስከ መካድ ድረስም እንኳን ሄዷል፡፡

የሙስሊም እምነትን ወክሎ የሚከራከረው ሻቢር አላይም ይህንን ቲዎሪ ትክክል ነው በማለት ለመመከት ሙከራን አድርጓል (በእርግጥ ባይሳካለትም) ይህንንም ያደረገው ከዶክትር ዊልያም ሌን ክሬግ ጋር ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2003 (እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር) በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ‹የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሞት በአካል ተነስቷልን?› በሚል ርዕስ ላይ ክርክር ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በተደረገው ጥቄዎችና መልስ ወቅት በቶኔ ኮስታ ጥያቄ ሲቀርብለት ሻቢር አላይ ወደ አይመዲያዎች ‹የመሳት-ፅንሰ› ሐሳብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ እሱም ይህ የአህመዲያዎች አመለካከት በጤናማዎቹ ሙስሊሞች እንደ ስህተት እንደሚቆጠር አይቶ የሚከተለውን ተናግሯል፡-

‹ሱኒ ሙስሊሞች ኢየሱስ ዳግም እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ ይህም እስከ ነቢዩ መሐመድ ድረስ በተነገሩት ብዙ ታማኝ መረጃዎች ስልጣንና ዘገባ መሰረት ትክክል ነው ይህም እንደ ቡካሪ ሙስሊም እና ወ.ዘ.ተ ላይ ግልጥ እንደሆነው ነው፡፡ የአህመዲያ ቡድኖች ኢየሱስ ድጋሚ አይመጣም ይላሉ ምክንያቱም የቡድኑን እንቅስቃሴ በመሠረተው ሰው በኩል ዳግም መጥቷል በማለት ያምናሉና፡፡ እኔ ኢየሱስ ድጋሚ እንደሚመጣ ነው የማምነው - በማለት ተናግሯል፡፡

አሁን የእኛ አቋም ኢየሱስ በመስቀል ላይ አልሞተም (ወይንም ከመሞት ተርፏል) ወደሚለው ነጥብ ላይ እየመጣና እየተጠጋ ነው፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች በአጠቃላይ የሚከተሉትን መረጃዎች ተመልክቻለሁኝ፡፡ ይህም በመስቀል ላይ ለኢየሱስ አንድ ሰው ተተክቶ ሞቷል የሚለውን ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ምንም እንኳን እጅግ በጣም ብዙ ማስረጃዎችና ሪፖርቶች ቢኖሩም እዚህ ጋ በትክክል ምን እንደሆነና ምትክ የሆነውም ሰው እንዴት እንደተሰጠ ተንታኞቹ በአንድ ሐሳብ ላይ መስማማት አይችሉም፡፡ እንዲሁም በኒአል ሮቢንሰን አስደናቂ ትንተና አማካኝነት እንደሚታየው ሁሉ  እነሱ እየተከተሉ ያሉት በኢራቅ ከጀመረ መረጃ ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ሙስሊሙ ኒአል ሮቢንሰን ‹ክርስቶስ በእስልምናና በክርስትና› የሚለውን መጽሐፍ የጻፈው ነው፡፡ እራሱን በእራሱ በመተርጎም ከሁሉም የተሻለ የሆነውን የቁራንን ጽሑፍ፣ እራሱን ስንመለከት የምናገኘው ነገር ክፍሉን የሚያጠቃልል ነው፣ ‹በእርግጥ እነሱ አልገደሉትም› በማለት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን አነሳው፡፡ ኢየሱስን በተመለከተ ምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ እኔ ይህንን የምወስደው ለነገሮቹ ሁሉ ማጠቃለያ አድርጌ ነው፡፡ እሱን ለመግደል በእርግጥ ሴራ ነበር፣ ነገር ግን እርሱን አልሰቀሉትም አልገደሉትምም፡፡ በአብዱል ማጅድ ዳርያባዲ አማካኝነት በታፍሲር አል-ቁራን ላይ የተሰጠው ትርጉም ይህ ነው፡፡ ይህም በቁርአን ላይ የተዘጋጀ የሱኒዎች ታፍሲር ነው፡፡ ስለዚህም እኔ በአቋሜ ላይ እንዳለሁ ነኝ እናም አቋሜንም አልለወጥኩኝም ነገር ግን ምናልባት አተረጓጎሜን ሊሆን ይችላል፡፡

ሦስተኛ፡- የአፈ ታሪክ ፅንሰ ሐሳብ The Legend Theory

ሦስተኛው ፅንሰ ሐሳብ ስቅለት አልተከናወነም ነገር ግን ቆይቶ በኋላ የተፈጠረ አፈ ታሪክ ወይንም ፈጠራ ነው የሚል ነው፡፡ ይህንንም የኋለኛው መሐሙድ አሳድ የሚያራምደው አመለካከት ነው፡፡

ስለዚህም ቁርአን ቁርጥ ባለ ሁኔታ የክርስቶስ ኢየሱስን የመሰቀል ታሪክ ይክዳል፡፡ በሙስሊሞች መካከል እጅግ ብዙ የሆኑ አስቂኝ አፈ-ታሪኮች ይገኛሉ፣ እነዚህም በመጨረሻው ደቂቃ ላይ እሱን በመሰለ ሰው ኢየሱስን እግዚአብሔር እንደተካው የሚናገሩ ናቸው፡፡ (በአንዳንዶቹ አባባል መሠረት ያ ሰው ይሁዳ ነው) እሱም በዒሳ ምትክ ተሰቅሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ አፈታሪኮች ውስጥ ማናቸውም በቁርአን ውስጥ ወይንም ደግሞ ተቀባይነት ባላቸው በልማዶች ውስጥ ቅንጣትም ድጋፍ የላቸውም፡፡ ስለዚህም በተንታኞች የተዘጋጁት ዋና ዋና ታሪኮች ይህንን በተመለከተ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ እነሱም የሚወክሉት በቁርአን ላይ ያለውን እና ኢየሱስ አልተሰቀለም የሚለውን ዓረፍተ ነገር በወንጌሎች ላይ ካለው የእሱ ስቅለት ስዕላዊ መግለጫ ጋር ለማዛመድ የተምታታ ሙከራን ለማቅረብ ሲሞክሩ ነው፡፡ የስቅለት ታሪክ በቁርአን ሐረግ ላይ በትክክል እንደተገለፀው የሚለው ‹ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣› ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ከኢየሱስ ዘመን፣ በጣም ብዙ ጊዜ ካለፈ በኋላ (በሆነ መንገድ) እንደ አንድ አፈ ታሪክ እየተስፋፋ እንደመጣ ነው (ምናልባትም በሚስራይስቲክ እምነቶች Mithraistic beliefs ኃይለኛ ተፅዕኖ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ‹Mithraistic beliefs በፐርሺያ የተጀመረ የሚስራስ ጣዖታት አምልኮ ነው›)፡፡ በዚህም መሠረት እያደገ የመጣው ሐሳብ ዒሳ የሞተው የተፈጥሮ ኃጢአትን [original sins] ስርየት (ይቅርታን) ለማስገኘት ነው፡፡ ሰው በተፈጥሮው ኃጢአተኛ ነው የሚባለው - የሰው ልጅ ተሸክሞታል ተብሎ በስህተት የሚነገረው ነገር ነው፡፡ እናም ይህ አፈ ታሪክ እጅግ በጣም በጥብቅ ተመስርቶ ቀጠለ ይህም በኋለኛው ጊዜ በነበሩት በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እና እንዲሁም በጠላቶቹም ጭምር ነው፣ ማለትም አይሁዳውያንን እንኳን ሳይቀር ጨምሮ ነው፡፡ እነሱም በእሱ ማመንን ጀመሩ ምንም እንኳን በማሾፍ መልክ ቢሆንም (ምክንያቱም ስቅለት በእነዚያ ጊዜያት እጅግ አሰቃቂ እንዲሁም ለዝቅተኛ እንስሳት የተመደበ ዓይነት የሞት ቅጣት ነበርና)፡፡ ስለዚህም ‹ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣› ለሚለው ለአዕምሮ አጥጋቢው የሚሆነው ገለጣ ምሳሌያዊ አነጋገር ሆኖ ‹ነገሩ ለእኔ የውሸት (እንደ ህልም) ምስል መሰለኝ› የሚለው ብቻ ነው፡፡ ማለትም በአዕምሮዬ በሌላ አነጋገር ‹ለእኔ መሰለኝ› ማለት ነው የሚሆነው፡፡ (see Qamas, art. khayala, as well as Lane II, 833, and IV, 1500).

አራተኛ፡- የተፈጥሮ ሞት ፅንሰ ሐሳብ The Natural Death Theory

ሞይዝ አምጃድ ይህንን ቲዎሪ ሲያስረዳ የተናገረው ቁርአን የሚያስተምረው ኢየሱስ ተፈጥሮአዊ ሞትን ሞቷል በማለት ነው ይላል Understanding-Islam.com፡፡

‹የኢየሱስን የመጨረሻ ሰዓታት በተመለከተ፣ በእርግጥም የሙስሊም ሊቃውንት እጅግ በጣም ግራ ተጋብተዋል በጣምም ተምታቶባቸዋል እርስ በእርስም ተከፋፍለዋል፡፡ የኢየሱስን የመጨረሻ ሰዓታት በተመለከተ የመጀመሪያዎቹ የሙስሊም ሊቃውንት አመለካከት አንድ ዓይነት አይደለም፣ አንዳንዶቹ ሊቃውንት ክርስቶስ በእርግጥ ሞቷል ሲሉ አንዳንዶቹ ግን ሳይሞት በቀጥታ ወደ ሰማይ እግዚአብሔር ወስዶታል ይላሉ፡፡ ይህንንም በተመለከተ ከቀደሙት ሊቃውንት መካካል የተለየ አመለካከት ካላቸው ውስጥ ምሳሌ የሚሆነን Abu Ja'far Muhammad b. Jarir al-Tabari (839-923)." ነው፡፡ የአል ታባሪ እና እሱ የሚያራምደው አመለካከትም ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና ወደ ሰማይም እንደተወሰደ ነው፡፡ (ጥንታዊው የሙስሊም ተንታኝ አል-ታባሪ ይከተለው ስለነበረው አመለካከት በሳም ሻሞን የተጻፈውንና Al-Tabari On the Birth, Life, Death and Ascension of the Lord Jesus Christ የሚለውን ጽሑፍ ትርጉም በቅርቡ ለአንባቢዎች እናቀርባለን፡፡) አል-ታባሪ የዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪከኛ (9th Century Muslim Historian, Al Tabari) እና ተንታኝ ነው፡፡

የሐዲት ስብስብ፡

በመጨረሻም ብዙዎቹ የሐዲት ስብስቦች ላይ ስንመጣ በተለይም ዋና ዋናዎቹ እና በጣም ታማኝ የሚባሉት ሁለቱ Sahih Bukhari and Sahih Muslim, ስቅለትን በተመለከተ ምንም የሚናገሩት ነገር አለመኖሩ ብዙዎችን ማስደነቅ ይኖርበታል፡፡ (ሐዲቶች ስለ ስቅለት የሚናገሩት ይህ ነው የሚባል ነገር የለም)፡፡

የችግሩ ማጠቃለያ፡

(የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ ሙስሊሞች እና በየጊዜው የተነሱ የሙስሊም ሊቃውንቶች አንድ ወጥ የሆነና በተጨባጭም ይህ ነው የሚባል እውነት አይከተሉም፡፡ የሚቀጥለው የማጠቃለያ ነጥቦች ጭብጥ የሚያሳየን ከላይ በቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ያሉትን ሰባት የተለያዩ አመለካከቶችን ነው)፡፡

1. የምትክነት ቲዎሪን የሚቀበሉት ሙስሊሞች፣ በክርስቶስ ምትክነት የተሰቀለው ሰው ማነው? በሚለው ሐሳብ ላይ ወደ ስምምነት መምጣት አይችሉም፡፡ አንዳንድ የሙስሊም ተንታኞች ማነው በክርስቶስ ምትክ የተተካው የሚለው ጋ ሲመጡ ፀጥ ነው የሚሉት (ይህም የሚያስታውሰኝ ምንም እርግጠኛ እውቀትና እውነት የሌላቸው መሆኑን ነው)፡፡

2. ሁሉም የምትክነት ታሪኮች ተመሳሳይነት የሌላቸው ናቸው፣ የእነሱም ዝርዝር ሁኔታ ልዩነቶች አሏቸው ስለዚህም በተንታኞች መካከል አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለ ይመስላል፡፡

3. የመጀመሪያው ዘመን እስላሞች ስለዚህ ነገር በጣም ዝምተኞች ይመስላሉ፣ የኢማም ቡካሪ እና የኢማም ሙስሊም የሐዲት ስብስብም እንኳን ስለ ስቅለት ጉዳይ ምንም የሚናገሩት ነገር የለም (ማለትም ፀጥ ብለዋል)፡፡

4. አንዳንድ ሙስሊሞች የሚያምኑት ኢየሱስ ተሰቅሎ እንደነበረና ነገር ግን በስቅላቱ መስቀል ላይ ሳይሞት እንደዳነ ከዚያም ወደ ሰማይ በአላህ እንደተወሰደ ነው ይህም ‹የመሳት ፅንሰ ሐሳብ› ወይንም ሱዉን ቲዎሪ የሚባለው ነው፡፡

5. አንዳንድ ሙስሊሞች ኢየሱስ በፍፁም እንዳልተሰቀለ ነገር ግን የተፈጥሮ ሞትን እንደሞተ፣ ሆኖም ግን አንድ ሰው በእሱ ምትክ እንደተሰቀለ ያምናሉ፡፡

6. አንዳንድ ሙስሊሞች የሚያምኑት ተሰቀለ የሚባል ሰው በጭራሽ እንዳልነበረ ይህም ኢየሱስ ወይንም ሌላ እሱን የሚመስል የሚባል ሰው እንዳልነበረ እናም ይህ የስቅለት ታሪክ በኋላ ቆይቶ በአይሁዶች የተፈጠረ አፈታሪክ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡

7. ጥንትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የእስላም ሊቃውንት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እንደተከፋፈሉ ነው፡፡ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ የሆነ ሲሆን፣ ስቅለትን በተመለከተ በአላህ ማህበረሰብ ውስጥ ይሄ ነው የሚባል አንድ ዓይነት ስምምነትና እውቀት እንደሌለ ነው፡፡

መደምደሚያ

አይሁዶችና ክርስትያኖች ግምት ብቻ እንጂ ምንም ሌላ ነገር የላቸውም በማለት መወንጀል በትክክል የሚመስለው ግብዝነት ብቻ ነው፡፡ በተለይም ተቃዋሚ ለሆነው ነገር ምንም ተጨባጭ የሆነን ማስረጃ በትክክል ሳይሰጥ እውነተኛ እውቀት ሊኖር አይችልም፡፡ ስቅለትን አስመልክቶ በትክክል ምን ሆነ? ለሚለው ነገር ትክክለኛ መግለጫ ሳይቀርብ፣ ቀጣዩ የሙስሊም ትውልድ ስለዚህ ነገር የራሱን የተለያየ አስተያየትና ትርጉም  እንዲሰጥ መተው ትክክለኛ አስተሳሰብና አመለካከት አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ማህበረሰብ ስለአንድ ነገር ግምትን እየሰጠ እያለ፣ ሌላውን በግምት ነው የሚመራው ብሎ መወንጀል ወይንም መተቸት ወጥነት የሌለው ነገር ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ሙስሊሞች ከሚቃወሟቸው ክርስትያናዊ እምነቶች መካከል አንዱ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ባየነው ጽሑፍ ውስጥ ግልፅ እንደሆነው ተቃውሞው መሠረታዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የሙስሊም ሊቃውንትም ሆኑ እራሱ ቁርአን ክርስትያኖችንና አይሁዶችን ያውግዙ እንጂ እራሳቸው ትክክለኛ መልስ የላቸውም ከግምትም ውጪ የሆነን ነገር አልተናገሩም፡፡ ስቅለትን በተመለከተ ከዚህ በላይ ያየናቸው አራቱ የሙስሊም ሊቃውንት ልዩ ልዩ ፅንሰ ሐሳቦች (ቲዎሪዎች) በትክክለኛ መረጃና በታሪክ ላይ ያልተመሰረቱ ግምቶች ብቻ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እውነት ፈላጊ የሆኑት ብዙ ሙስሊሞች ሕይወት ከፈጣሪ እውነተኛ የደኅንነት ሕይወትና የዘላለም ዕቅድ ውጪ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ 

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀልና መሞት ለሰዎች ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ የታቀደውም የተከናወነውም በእግዚአብሔር ፈቃድ በጌታ በኢየሱስ በራሱም ፈቃድ ጭምር ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የመሞቱ እውነታ በክርስትያን ጽሑፎች፣ በወንጌል ውስጥ በተመዘገቡ የዓይን ምስክሮች፣ እንዲሁም በዓለም ታዋቂና ተቀባይነት ባላቸው የታሪክ ጸሐፊዎች ዘገባዎች ሁሉ ውስጥ የተመዘገበና በታሪክ እርግጠኛ የሆነ ነገር ነው፡፡

እውነትን በትክክል ለመረዳት የሚፈልግ ሙስሊም ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስንና ታሪክን በማንበብ እውነቱን እንዲረዳ እንጋብዘዋለን፡፡ ከሁሉ በላይ ለአንድ ሰው እጅግ ጠቃሚ የሆነውና እኛም እራሳችን በተግባር በሕይወታችን ያየነው ነገር አንድ ሰው ከኃጢአት የዘላለም ቅጣት ነፃ የሚሆነው በክርስቶስ በኩል ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ኃጢአታችሁን ተናዛችሁ ወደ ክርስቶስ ብትመለሱ ከእሱም ዘንድ ቀርባችሁ እውነተኛ ንስሐን ብትገቡ ደግሞም እሱ በመስቀል ላይ በከፈለው የኃጢአት ዋጋ ብትታመኑ ድንቅ የሆነ የሕይወት ለውጥ ታገኛላችሁ፡፡ የእግዚአብሔርም ልጆችና የመንግስቱ ወራሾች ትሆናላችሁ፡፡ እግዚአብሔር በፀጋውና በኃይሉ ሁሉ ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: The Confusion of Islam regarding the Crucifixion of Jesus Christ, Derik Adams

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ