መንግስተ ሰማይ በቁርአን

M. J. Fisher, M.Div.

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለክርስትያኖች ተስፋ በተገባው መንግስተ ሰማይና በቁርአን ውስጥ የተገለጠው ፓራዳይዝ ወይንም ገነት መካከል እጅግ በጣም ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ታዲያ የትኛው ነው እውነተኛ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ ይችላሉን?

ዘላለማዊ ሕይወት በማለት ክርስትያኖች የሚጠሩት በቁርአን ውስጥ መንግስተ ሰማይ ተብሎ አልተጠራም፡፡ የሙስሊሞች የሰማያዊው መንግስት ሽልማት ፅንሰ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው እውነታ ጋር እጅግ በጣም የተለያየ ነው፡፡ የሙስሊሞችን የገነት መንግስተ ሰማይ በተሻለ ሁኔታ ለማብራራት እንዲቻል 37 የሚሆኑ የቁርአን ጥቅሶች አጠር ባለ መልኩ እዚህ ጽሑፍ ውስጥ ተጠቅሰዋል፡-

ቁርአን እነዚህን ገነቶች የስጋ ደስታ የሚታይባቸው የአትክልት ቦታዎች አድርጎ ነው የሚጠቅሳቸው፡፡ ከእነዚህም ደስታዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በዚህ ምድር ላይ ለእስላሞች የተነፈጓቸው እንደሆኑ ተደርጎም ነው የቀረበው፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሙስሊም ወንዶች በአንድ ጊዜ የሚኖሯቸው ሚስቶች የተወሰኑ ነበር:: ነገር ግን ቁርአን ቃል ኪዳን የሚገባው እጅግ ቁጥር የሌላቸው ልጃገረዶች በጣም በተጠበቁ ድንኳኖች ውስጥ ምቾት ባላቸው መቀመጫዎችና አልጋዎች ላይ ሆነው እንደሚጠብቋቸው ነው፡፡ ሌላው በምድር የተነፈጉት ነገር አልኮል መጠጣት ነው፡፡ በዘላለማዊው ገነት ውስጥ ልክ የሌለው የወይን ጠጅ ይሰጣቸዋል፣ የወይን ጠጆቹም ምንም ጉዳት የማያመጡ ስለሆኑ እንደፈለጉት ይጠጧቸዋል፡፡ የገነቶቹም ነዋሪዎች ሁልጊዜም ምስጋናን የተሞሉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው የመንግስተ ሰማይ ምስል ግብረስጋዊ ግንኙነትን በፍፁም አይጨምርም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግልፅ እንዳደረገው በመንግስተ ሰማይ ያሉት እነዚያ አይጋቡም ነገር ግን ልክ እንደ መላእክት ይሆናሉ (ማቴዎስ 22.30) በማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ወጥነት ያለው የመንግስተ ሰማይ አገላለጥ እግዚአብሔርን ማምለክ እንዲሁም ከየወገኑና ከየቋንቋው ከዳኑት ህዝብ ጋር ህብረትን ማድረግ ነው (ራዕይ 7.9)፡፡

መንግስተ ሰማይን በተመለከተ ቁርአን የሚከተሉትን ነገሮች ይናገራል፡-

የሰው ስጋዊ ፍላጎቶች ይሟላሉ፡- ከሞት በኋላ ያለው የሙስሊሞች ሕይወት ፍላጎቶቻቸው ሁሉ የሚሟሉበት ቦታ ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ ነገር የሚሆንላቸው ቦታ ነው 50.35፡፡

ማለቂያ የሌለው የወይን ጠጅ ምንጭ፡- ፃድቃኖቹ ማለቂያ ከማይኖረው የወይን ጠጅ ምንጭ ይጠጣሉ ይህም ከካፉር ውሃ ጋር የተደባለቀ ነው (76.5-6)፡፡ እሱም ነጭ ወይን ነው የሚሆነው ነገር ግን በበረከት ገነት ውስጥ የሚኖሩትን አስካሪ አይሆንም 37.45-47፡፡

አትክልት ቦታዎች፡- ከሞት በኋላ የሚሆኑት ደስታዎች ከሁሉም ዓይነት ስጋዊ ደስታዎች በተሞሉት በሁለት የአትክልት ቦታዎች ውስጥ ነው የሚሆኑት 55.46-48፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ አትክልት ቦታዎች አሉ እነሱም ደስታዎችን የተሞሉ ናቸው 55.62፡፡

ደናግል፡- በአትክልት ቦታዎቹ ውስጥ ፍራፍሬዎች፣ ጥላ ቦታዎች፣ የውሃ ፏፏቴዎች እና ደናግል የሞሉባቸው ናቸው፡፡ ደናግሎቹም ደግሞ ዓይናፋርና እንደ (ያቁትና መርጃን ይመስላሉ እነዚህ ለጌጥ የሚሆኑ የሚያንፀባርቁ ክብር ድንጊያዎች ናቸው) 55.56፣ 58፡፡ እንዲሁም በሁለተኛው ገነት ውስጥ ደግሞ ጥቁር ዓይን ያላቸው ሰማያዊ አጃቢዎች ይኖራሉ እነሱም በትላልቅ ድንኳኖቻቸው ውስጥ እንዲቀመጡ ይገደዳሉ፡፡ ሰዎችም ሆኑ ጅኒዎች አልገሰሷቸውም፡፡ የነሱም ንፅህና ገነት መግባት የተሰጣቸው ገነት እስከሚደርሱ ድረስ የተጠበቀ ነው፡፡ እነሱም በአረንጓዴ አረግራጊ ምንጣፎችና ስጋጃዎች ላይ የተደላደሉ ሆነው ይጠባበቃሉ 55.76፡፡ እነዚያም የተጨጎሉት እኩያዎች እና ጡተ ጉቻማዎች ናቸው 78.33፡፡ በገነት ውስጥ ሙስሊሞች ከተጨጎሉት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነትን ያደርጋሉ እነሱም ትላልቅ ውብ የሆኑ ጥቁር ዓይኖች አሏቸው 52.20፤ 44.54፣ 2.25፡፡ ዓይናፋር የሆኑ ደናግሎች ይከቧቸዋል ልክ እንደ እንቁላል የሆኑ ትላልቅ የሚያምሩ ዓይኖች ያሏቸው ናቸው 37.48-49፡፡

ቆንጆ የሆኑ የወንድ ሰራተኞች፡- እነሱም የሚገለገሉት እንደ እንቁ ቆንጆ በሆኑ ወጣት ወንዶች ልጆች ነው፡፡ እነሱም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ይጠብቋቸዋል፡ 52.24፡፡

መብልና መጠጥ፡- በአትክልቱ ቦታ በከፍተኛው ላይ ሙስሊሞች እስከ ልባቸው ጥግ ድረስ ይበሉና ይጠጣሉ 69.24፡፡

ምስጋናና ሕብረት፡- በገነት ደስታ ውስጥ ወንዞች በነዋሪዎቹ እግር ድረስ ይፈሳሉ፡፡ እነሱም በደስታ ይጮኻሉ እርስ በእርስም ሰላምታን ይሰጣጣሉ እንዲህም ይላሉ ‹ሰላም› 10.9-10፡፡ እነሱም ቀንና ሌሊት ሳይታክቱ ውዳሴን ይሰጣሉ 41.38፡፡

ወርቅና ሐር፡- እነዚያ በዘላላም ገነት ውስጥ ያሉት በወርቅ የእጅ አምባርና በቀጭን አረንጓዴ ሐር ልብስ ያጌጣሉ እነዚህም በሐር ላይ በወርቅ በተጠለፉ ስራዎች ነው 18.31፣ 35.33፡፡

ምድራዊ ሚስቶችና ቤተሰቦች፡- የእስልምናን እምነት የሚከተሉ ልጆች ያሏቸው ሙስሊሞች በበረከት የገነት ቦታ ላይ ከልጆቻቸው ጋር ይገናኛሉ ይህም በምድር ላይ እያሉ የሰሩትን እንዳያጡ ነው 52.21፡፡ ሙስሊሞች በኤደን ገነት ውስጥ የሚገቡት እስልምናን እንደተከተሉት እንደ አባቶቻቸው፣ ሚስቶቻቸው እና ልጆቿቸው ነው 13.23፡፡

ትልልቅ የመኖሪያ ቤቶች፡- ይህ በአላህና በመሐመድ ማመን ያታዘዘ ነው፡፡ በሁሉም ነገር ስለ እስልምና መዋጋትና መጋደል የታዘዘ ነገር ነው፡፡ በሕይወትም እንኳን ቢሆን ስለዚህም ኃጢአቶቻቸው ይቅር ይባልላቸዋል እንዲሁም በገነት አትክልት ቦታ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል ትልልቅ የመኖሪያ ቤትም ይሰጣቸዋል 61.11-12፡፡ እንዲሁም እነዚያ የሚገባቸው፣ ወንዞች በስራቸው የሚፈሱላቸው ሰፋፊ ቤቶች ይሰጣቸዋል 39.20፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

የመንግስተ ሰማይ ጉዳይ የምር ጉዳይ ነው፡፡ ለዘላለም ከሞት በኋላ ስለምንኖርበት ቦታ ስለ መንግስተ ሰማይ ትክክለኛ እውነት ላይ የተመሰረተ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ አማኞች በመንግስተ ሰማይ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ መንግስተ ሰማይ ቅዱስ እና ፍፁም ስፍራ ናት፡፡ መንግስተ ሰማይ መግባት የሚቻለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በመንግስተ ሰማይ ሰዎች በዘላለም በደስታ እግዚአብሔር ፊት እንደሚኖሩ ሲናገር፣ በምድር የሚገኙት ዓይነት ግብረስጋ ግንኙነትና መጠጥ መጠጣቶች በሠራተኞች መገልገል የሚባሉ ነገሮች የሉበትም፡፡ ስለ መንግስተ ሰማይ በትክክል ማወቅ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም መቅደም ያለበት ግን መንግስተ ሰማይ መግባት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ መልስ ነው፡፡ አንባቢ ሆይ አንተ/ቺ የዚህን ጥያቄ መልስ በትክክል ታውቁታላችሁን? በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው እምነታቸውን በእሱ ላይ ያደረጉ ሰዎች ሁሉ ለዚህ ጥያቄ እርግጠኛ መልስ አላቸው፡፡ እንዴት አወቁት፣ እንዴት እርግጠኞች ሆኑ?

እናንተም ስለ መንግስተ ሰማይ በትክክል ለማወቅ እንድትችሉ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡ እና ትክክለኛውን ግንዛቤ እንድትይዙ፣ ስለ ዘላለምም ሕይወት የምርነት እንድታስቡ ጌታ ኢየሱስ በፀጋው ይርዳችሁ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Paradise, Chapter 9 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ